ትምህርቶች(To Read)

ከመታወቅ በላይ የሚሆነውን የክርስቶስን ማንነትና ምስጢር ለመናገር ባሰብኩ ጊዜ ሁሉ ውስጤ ይናወጣል:: በአንድ በኩል የእግዚአብሔርን ልጅ የክርስቶስን ማንነት ለመናገር እግዚአብሔር አምላኬ ስላበቃኝ፣ ይህንን አውቀን የማንጨርሰውን፣ ከማስተዋልም በላይ የሆነውን፣ ተመርምሮ የማይዘለቀውን የእግዚአብሔርን ልጅ ምስጢር በጥቂቱም ቢሆን ሊያስታውቀኝ ስለወደደ እግዚአብሔርን አመሠግነዋለሁ:: በዚህም ደግሞ እጅግ ደስ ይለኛል::

     በሌላ በኩል ግን ያሉኝ ቃላቶች፣ የማውቃቸው የመግለጫ ዓ/ነገሮች ሁሉ እጅግ ስለሚያንሱ፣ እጅግም ውሱን ስለሆኑ፣ የእግዚአብሔርን ልጅ ይገልጹት ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ጥበብ ያስታውቁ ዘንድ አይችሉምና በዚህ አዝናለሁ:: ስለ ሌላ ስለማውቃቸው ምድራዊ ነገሮች እንድናገር የተጠየቅሁ ቢሆን ኖሮ ቶሎ መልስ ለመስጠትና ፈጥኜ ለመናገር በቻልኩ ነበር:: ነገር ግን ይህን ከእግዚአብሔር ዘንድ የተገለጠውን የክርስቶስን ማንነትና ክብር በቃላት ለመግለጽ እጅግ ስለሚከብድ ከመናገሬ በፊት ብዙ አስባለሁ፣ የእግዚአብሔርንም ታላቅ እርዳታ እሻለሁ::

     በዚች ጹሑፍም ከአእምሮ የሚያልፈውን እጅግ ጥልቅ የሆነውን የክርስቶስን ማንነትና ክብር ከዮሐንስ ወንጌል እግዚአብሔር እንደረዳን መጠን አብረን እንመለከታለን:: አንተም ደግሞ ይህንን ጽሑፍ በእጅህ የያዝክና የምታነብ፣ እግዚአብሔር የራሱን ምስጢር፣ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲገልጥልህ፣ ጌታም ራሱን እንዲያሳውቅህ አምላኬን እለምናለሁ:: በአእምሮ የማውቀውን እውቀት ብቻ አይደለም የምነግርህ:: የክርስቶስ ነገር በጽሑፍ ብቻ የሚገለጥ አይደለም:: በአእምሮችን ብቻ የምንይዘው ነገር አይደለም:: የክርስቶስ ማንነት በሕይወታችን ሁሉ ጠልቆ ሊገባ የሚያስፈልግ፣ በግል ለእያንዳንዳችን ራሱን ካልገለጠልን ፈጽሞ ልናውቀው የማንችለው፣ እጅግ ድንቅ የሆነ የእግዚአብሔር ምስጢር ነው::

"በፍቅርም ተባብረው በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ሁሉ እንዲደርሱ፣ የእግዚአብሔርንም ምስጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ እጋደላለሁ::" ቆላ 2፣2

     ብዙ የእግዚአብሔር ነቢያትና አገልጋዮች የእግዚአብሔርም ባሪያዎች ባላቸው ቃላት የእግዚአብሔርን ልጅ ማንናት በመግለጽ ለኛ አስተላልፈዋል:: በተላያየ ሁኔታና ጥበብ በተለያየም መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ ነቢያቱና አገልጋዩ ሁሉ ስለ ክርስቶስ መስክረዋል:: ከነዚህም ውስጥ እጅግ በተለየ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ልጅ በቅርበትና በጥልቀት የገለጠውን ሐዋሪያው ዮሐንስ ነው:: እንግዲህ ወገኔ፣ አንተና እኔ አብረን ከዮሐንስ ጋር የኢየሱስ ክርስቶስን ጥልቅ ምስጢር እንድንመለከትና እንድንረዳ አብረንም ደግሞ ክብሩን እንድናይ እጋብዝሃለሁ:: ልብህና አእምሮህ ለእግዚአብሔር ቃል የተከፈተ እንዲሆን እግዚአብሔር አምላኬን እለምነዋለሁ:: የእግዚአብሔርን ልጅ ድንቅ የሆነ ሰማያዊ ክብር ሊገልጽ የሚችል እግዚአብሔር እራሱ ብቻ ነውና::
     ሥጋና ደም፣ የሰው ጥበብና ብልሃት፣ የሰውም እውቀት የኢየሱስን ጥልቅ ሚስጢር ሊገልጽ ስለማይችል፣ የተወደደው አምላካችንና አባታችን ልጁን ለአንተ አብልጦ እንዲገልጽልህና እንዲያስታውቅህ ጸሎቴ ነው::

     ለአንተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ እኔ አላውቅም፣ በአይንህ ፊት ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ፣ እንዴት አድርገህ እንደምትረዳው እኔ አላውቅም:: ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ዘመን ግን ብዙዎች በተለያየ ሁኔታ ኢየሱስን ይመለከቱት ነበር:: አንድ ጊዜ ኢየሱስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ላይ እንዲህ ብሎ ደቀመዛሙርቱን ጠየቃቸው::

"ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል... እነርሱም:- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት:: እርሱም እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው:: ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ:- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ::" ማቴ 16፣13-16

     በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች ይህንን የተገለጠውን የእግዚአብሔር ታላቅ ምስጢር፣ ይህንን ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተላከውን ድንቅ፣ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ከነቢያት አብልጠው ሊያዩ አልቻሉም ነበር:: አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው... ወዘተ ይሉ ነበር:: ከነብይ ግን የሚበልጥ ሌላ ነገር አይታይበትም ማለታቸው ነው:: ነብያት ተዓምራት ያደርጋሉ እርሱም ተዓምራት ያደርጋል:: እነርሱ ያስተምራሉ እርሱም ያስተምራል:: ነብያት የእግዚአብሔርን ቃል ለሕዝብ ያመጣሉ እርሱም ያመጣል:: ክርስቶስን ግን ከዚህ አብልጠው ሊያዩ አልቻሉም::

     ወገኔ ሆይ፣ ዛሬም ቢሆን ሰዎች ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተለያየ አመለካከት አላቸው:: አንዳንዶች መልካም ሰው ነበር:: ሌሎች ጥሩ አስተማሪ ነበር:: ነብይ ነበር፣ ሌላም ሌላም ይላሉ:: ነገር ግን የእግዚአብሔርን ልጅ ማንነቱን በቅርበት፣ ክብሩንም በሙላት ገና አልተረዱም:: ከነብይና ከአስተማሪ አብልጠው ሊያዩት ይከብዳቸዋል::

     ኢየሱስ ሰዎች ስለ እርሱ የሚሉትን ከሰማ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ፣ ወደሚከተሉትና እናውቅሃለን ወደሚሉት ዘወር ብሎ:- "...እናንተስ እኔን ማን እንደሆንሁ ትላላችው? አላቸው:: ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ:- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ::" ማቴ 16፣15-16

     ዛሬስ አንተን ስለ ማንነቱ ቢጠይቅህ የምትሰጠው መልስ ምን ይሆን? አንተስ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ትላለህ? እንደ ደቀመዛሙርቱ በቅርበት ተረድተኸዋል ወይስ በርቀት እንዳሉት እንደ ሌሎቹ ከነብያትና ከሃይማኖት መሪዎች ትመድበዋለህ? ጥሩ አስተማሪ ብቻ ነው ለአንተ? መምህር ብቻ ነው? ነብይ ብቻ ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንተ ማነው? አንተስ እርሱ ማን እንደሆነ ትላለህ? በጥልቀት የእግዚአብሔርን ልጅ አውቀኸው ይሆን? ይህንን ከእግዚአብሔር የተገለጠ ድንቅ ምስጢር አንተስ ዛሬ ማን ትለው ይሆን? እኔ አላውቅም::

     ነገር ግን ዛሬ ከዮሐንስ ወንጌል፣ ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ማንነት፣ ከመታወቅ የሚያልፈውን የኢየሱስን ባለጠግነትና ክብር፣ አብረን እንድንመለከት እጋብዝሃለው:: እግዚአብሔር ደግሞ እንደሚናገርህና ራሱንም እንደሚገልጽልህ አምናለው:: ይህን ድንቅ ለሰዎች የገለጠ አምላክ ስሙ የተባረከ ይሁን!

     ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በተመላለሰ ጊዜ ስዎች ስለ እርሱ የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም ዮሐንስ ግን ለየት ባለ ሁኔታና በቅርበት የእዚአብሔርን ልጅ ማንነት ሲገልጸው እንመለከታለን:: ለዮሐንስ እየሱስ ክርስቶስ ነብይ ብቻ አልነበረም፣ ነገር ግን አለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ የእግዚአብሔር ቃል ነው:: የዮሐንስ ወንጌልን ገና የመጀመሪያውን ምዕራፍ ማንበብ ስንጀምር ዮሐንስ የክርስቶስን ማንነት እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል::

"መጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ:: ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ:: ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም::" ዮሐ 1፣1-3

ወረድ ብለን ደግሞ በቁጥር 14 ላይ ስንመለከት የዚህን ቃል ማንነት እናያለን:-

"ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን::" ዮሐ 1፣14

     ይህ በመጀመሪያው የነበረው ቃል ከአባቱ ክብርን ለብሶ፣ ሥጋ ሆኖ የመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ዮሐንስ ይገልጽልናል:: ዮሐንስ ስለዚህ ቃል ወይም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጽ ሲጀምር "በመጀመሪያው" የሚለውን ቃል በማስቀደም ነው:: በመጀመሪያው ቃል ነበር ይላል:: ገና ከፍጥረት በፊት፣ ገና የሚታዩና የማይታዩ ነገሮች ከመፈጠራቸውና ከመከሰታቸው በፊት፣ ገና ምንም ነገር ከመኖሩ በፊት ይህ ቃል ነበረ:: ቃል ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ያልነበረበት አንዳችም ጊዜ አልነበረም:: ከእርሱ በፊት ምንም ነገር አልነበረም ምክንያቱም እርሱ በመጀመሪያው ላይ ነበረና:: ገና በጅማሬው ላይ ቃል እንደነበረ ዮሐንስ ይነግረናል:: ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድርና ሰማይ ከመፈጠራቸው በፊት ከእግዚአብሔር ጋር ይኖር እንደነበር ያሳየናል:: ፍጥረት የመጣው በኋላ ነው:: "ሁሉ በእርሱ ሆነ" ዮሐ 1፣3 ይላል፣ ፍጥረት ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለተፈጠሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተፈጠሩት ነገሮች እንደማይጠቃለል ያስረዳናል:: መፍጠር ወይም መፈጠር ከመጀመሩ በፊት ይህ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ ነበረ:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራዕይ መጽሐፍ ላይ ስለ ራሱ ሲናገር በመጀመሪያ ላይ የነበረ ብቻ ሳይሆን ራሱም መጀመሪያ እንደሆነ ይጠቅሳል::

"አልፋና ዖሜጋ፣ ፊተኛውና ኋለኛው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ::" ራዕይ 22፣13

     እዚህ ላይ አልፋና ዖሜጋ የሚለው ቃል የግሪኩን የመጀመሪያ ፊደል ማለትም አልፋን "A"፣ የመጨረሻውንም ፊደል ዖሜጋን "W" የሚያመለክት ነው:: ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም:- እኔ የመጀመሪያው ነኝ ብሎ መናገር አይችልም:: ከእርሱ በፊት ፈጣሪ ስላለ፣ ከእርሱ በፊት አምላክ ስላለ፣ ከእርሱም በፊት እርሱን የፈጠረው ጌታ ሰላለው፣ ማንኛውም ፍጡር:- እኔ መጀመሪያው ነኝ ማለት አይችልም:: ማንኛውም ነብይ ወይም የሃይማኖት መሪና አስተማሪ፣ ባጠቃላይ ማንኛውም ሰው ወይም መልአክ እንደዚህ ብሎ ሊል አይችልም:: ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እኔ የመጀመሪያው ነኝ ብሎ ይናገራል:: ከፍጥረትና ከጊዜያት ሁሉ በፊት እኔ ነበርኩ ይላል:: ይህም እርሱ ፈጣሪ አምላክ እንጂ ተፈጣሪ እንዳይደለ ያሳየናል:: እኔ የመጀመሪያው ነኝ ብሎ መናገር የሚችል፣ ራሱ አምላክ የሆነና ከእርሱም በፊት ምንም ያለነበረ ብቻ ነው::

     ከጊዜአትና ከቀናት በፊት በዓይን የሚታዩ ግዙፋንና በዓይንም የማይታዩ ጥቃቅን ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት ሕዋና ከዋክብት፣ ጨረቃና ፀሐይ፣ ሰማይና ምድር፣ ባሕሩና ተራራው፣ ሜዳውና ሸለቆው፣ እንስሳትና አራዊት፣ እፅዋትና አበቦች፣ በሰማያዊ ሥፍራ የሚኖሩ መላእክትም ጭምር ከመፈጠራቸው በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ነበረ::

     ኢየሱስ አንድ ጊዜ ለአይሁዶች እንዲህ አላቸው፣

"አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሴት አደረገ አየም ደስም አለው::" ዮሐ 58፣56

የጌታን ማንነት ያልተረዱና ጥልቅ ምስጢሩ ያልገባቸው አይሁድ ግን

     "...ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን? አሉት::"
ዮሐ 8፣57

ያ ዘመን አብርሃም ከኖረበት ዘመን ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ይራራቅ ነበርና::

"ኢየሱስ፣ እውነት እውነት እላችኋለው፣ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ አላቸው::" ዮሐ 8፣58

     ኢየሱስ ክርስቶስ በእነርሱ ፊት እንደሚመላለስ፣ በሥጋም የ30 ዓመት ሰው እንደሆነ ብቻ ነበር የሚያውቁት:: ነገር ግን ያ በፊታቸው የሚመላለሰው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት፣ አባታችን የሚሉትም አብርሃም ከመወለዱ በፊት እንደነበረ ገና አልተረዱም ነበር::

     በሌላ ቦታ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ኢየሱስ ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ እንዲህ አለ፣ "አሁንም፣ አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ::" ዮሐ 17፣5

     ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ፣ ዓለም ሳይፈጠር በፊት እንኳን በታላቅ ክብር ከእግዚአብሔር ጋር እንደነበረ ይናገራል:: ዮሐንስም ሊገልጽልን የፈለገው ነገር ይሄ ነው:: ኢየሱስ የዚህ ዓለም ውጤት አይደለም:: ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ኢየሱስ ነበረ:: አብርሃም ከመወለዱ በፊት ክርስቶስ ነበረ:: አዳም ከመበጀቱ በፊት እርሱ ነበር:: ኢየሱስ የተፈጠረ ስላየደለ ከፍጥረት በፊት ነበረ::

በዮሐንስ ወንጌል ይህ ቃል በመጀመሪያ የነበረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በተጨማሪም ይህ ቃል በመጀመሪያ ከማን ጋር እንደነበረ ተገልጿል::

     "ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር::" ዮሐ 1፣1

ይህንን ዓ/ነገር ዮሐንስ በቁጥር ሁለት ላይም ይደግመዋል::

     "ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ::" ዮሐ 1፣2

ሥጋ ሆኖ የመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከአብ ጋር በአንድ ኅብረት ይኖር ነበር:: ኢየሱስ ክርስቶስን ከሌሎች ነብያት፣ ከሌሎች አስተማሪዎችና የሃይማኖት መሪዎች እጅግ የሚለየው ነገር አንዱ ይሄ ነው:: ከሁሉም በፊት ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የነበረ፣ እግዚአብሔርንም በትክክል የሚያውቀው እርሱ ብቻ መሆኑ ነው:: በምድር ላይ የኖሩት ሰዎች የሁላቸውም፣ የትንሹም የትልቁም፣ መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው አፈር እንደሆነ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል::

     "እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው..." ዘፍ 2፣7

     "...አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህና::" ዘፍ 3፣19

     የየትኛውም የሃይማኖት መሪና ነብይ ጅማሬው አፈር ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስን ግን የሚለየው፣ እርሱ ከአፈር የመጣ ወደ አፈርም የሚመለስ ሳይሆን ከሰማይ ለሰው ልጆች የተገለጠ፣ ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የነበረና እግዚአብሔርንም በትክክል የሚያውቀው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ነው::

"ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለው፣ ደግሞ ዓለምን እተዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ::" ዮሐ 16፣28

     ኢየሱስ ክርስቶስ ከምድር የሆነን የሕብረተሰብን አስተሳሰብ እንዲሁም የሰውን ብልሃትና እውቀት፣ ከምድር የሆነ የፖለቲካ ሃሳብ፣ ከምድርም የሆነ የሃይማኖት ሥርዓትን አይደለም ይዞልን የመጣው:: ነገር ግን ከሰማይ የመጣው ወደ ሰማይ የሄደው ኢየሱስ በአባቱ ዘንድ ያየውንና የሰማውን ፍጹም ሰማያዊ ምስጢር ነው የገለጸልን:: ብዙ የሃይማኖት መሪዎች በዓይናቸው ስላላዩትና ስለማያውቁት እግዚአብሔር ብዙ ነገር ተናግረዋል:: ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አብሮት ከእርሱ ጋር የነበረውን፣ በቅርበት የሚያውቀውን አባቱን እግዚአብሔርን ነው ያሳየን::

"...ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል:: ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው:: ያየውንና የሰማውንም ይህን ይመሰክራል..." ዮሐ 3፣31-32

ስለዚህም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1 ቁጥር 18  ስንመለከት ይህን እናገኛለን::

"መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው::"

እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው:: አንድ ሰው ስንኳ፣ አንድ ነብይ ስንኳ፣ አንድ የሃይማኖት መሪና አስተማሪ ስንኳ፣ አንድ ስንኳ እግዚአብሔርን ያየው የለም:: እነዚህ ሁሉ ስለ እግዚአብሔር አስተምረው ይሆናል፣ ነገር ግን እግዚአብሔርን አላዩትም:: ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ በአባቱ እቅፍ የነበረው ልጁ ግን ተረከው:: በአባቱ እቅፍ የነበረ፣ አባቱን በትክክል የሚያውቅ አንድያ ልጁ፣ ያየውንና የሰማውን  መሰከረ::

ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔርን የገለጸና ያስታወቀ ማንም የለም::

"ወልድንም [ልጁንም] ማን እንደሆነ ከአብ [ከአባት] በቀር የሚያውቅ የለም፣ አብንም ማን እንደሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም..." ሉቃ 10፣22

     በዕብራውያን መልእክት ላይም እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ለእስራአኤል በነብያት እንደተናገረና በዚህ በመጨረሻው ዘመን ግን የራሱ ባህርይ ምሳሌ በሆነውና ዓለማትንም በፈጠረበት በልጁ እንደትናገረን ይገልጻል:: ዕብ 1፣1-3 በዚህ በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሔር መልዕክት ክርስቶስ ነው:: ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ይዞ የመጣ ነብይ ሳይሆን፣ ራሱ የእግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ እንዲሁም ባህርይ የተገለጠበት የእግዚአብሔር የመጨረሻ መልዕክት ነው:: በዚህ በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር ወደ ሰዎች የላከው የእርሱን ቃል ይዘው የሚመጡ ነብያትን ሳይሆን፣ ራሱ ሕያው ቃል የሆነውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው:: የእግዚአብሔር ሙሉ ቃልና ፈቃድ፣ ሙሉ ሃሳብና ባህርይ፣ ባጠቃላይ የእግዚአብሔር ማንነት በሙላት የተገለጠው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው የእግዚአብሔር መልዕክት ነውና:: "መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው::" ዮሐ 1፣18

ወገኔ ሆይ፣ እግዚአብሔርን በትክክል ማውቅ ትፈልጋለህ? እግዚአብሔርን በሙላት መረዳት ትፈልጋለህ? ኢየሱስ ክርስቶስን ጠጋ ብለህ በቅርበት ተመልከት!

     ምንም አይነት ሃይማኖት እግዚአብሔርን አይገልጽልህም:: ማንኛውም የሃይማኖት መሪ እግዚአብሔርን አያሳውቅህም፣ ራሱም እንኳን አላየውም:: የትኛውም ነብይና አስተማሪ እግዚአብሔርን በሙላትና በትክክል አይገልጥልህም:: እግዚአብሔርን የምታውቀው ብቸኛ የሆነውን፣ በእግዚአብሔር እቅፍ የነበረውን ኢየሱስ ክርስቶስን ስታውቅና ስትረዳ ብቻ ነው::

ወገኔ ሆይ፣ ምናልባት እስከ ዛሬ ድረስ ኢየሱስን እንደዚህ አልተመለከትኸው ይሆናል:: ምናልባት ይሄ ሁሉ አይበዛም ወይ? ትል ይሆናል:: ምናልባትም ካሰብከውና ከጠበቅከው በላይ ሆኖብህ ሊሆን ይችላል:: ሆኖም ግን ዮሐንስ በዚህ አያበቃም:: በዮሐንስ ወንጌል ገና ከዚህ የሚበልጥ የሚያስገርም ነገር እናገኛለን:: ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ መሆኑ ያስገርመን ይሆናል:: በእግዚአብሔር ዘንድ በኅብረት ያለ መሆኑና ከእርሱም በቀር እግዚአብሔርን ያየና በሙላት የሚያውቅ አለመኖሩ ያስደንቀን ይሆናል:: ነገር ግን ዮሐንስ፣ ቃል ራሱ ደግሞ አምላክ እንደሆነ ይነግረናል::

"....ቃልም እግዚአብሔር ነበረ::" ዮሐ 1፣1

ቃልም ራሱ አምላክ ነው ይለናል:: የኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነትንና አምላክነትን ዮሐንስ በግልጽ ያሳየናል:: ዛሬ አንዳንድ ግለሰቦችና ሃይማኖቶች (በኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን እናምናለን የሚሉ)፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በመካድ ላይ ይገኛሉ:: ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ በታቸ እንደሆነ ይባስ ብለውም እንደኛ የተፈጠረ ፍጡር እንደሆነ አድርገው የሚናገሩ አሉ:: አንተ ግን የዮሐንስን ምስክርነት ስማ! አንተ ግን የእግዚአብሔርን ቃል ተቀበል! አንተ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚልህን እመን! ቃሉ ምን ይላል?

"ቃልም እግዚአብሔር ነበረ::" ይላል:: ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ እንደሆነ ሳይሸፋፍን ይነግረናል:: አንተ ግን የእግዚአብሔርን ቃል ስማ! ቃሉ ምን ይላል?

ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር መልክ፣ ከእግዚአብሔር ጋርም በእኩል ደረጃ አምላክ ሆኖ ይኖር እንደነበር፣ ነገር ግን የሰው ልጆችን ለማዳን ራሱን አዋርዶ የሰውን መልክ እንደያዘ ይነግረናል::

"እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ..."ፊል 2፣6-8
    
ወገኔ ሆይ፣ አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ! ወደ ግራም ወደ ቀኝም አትበል፣ ነገር ግን ጆሮህን ወደ ቃሉ አዘንብል! ቃሉ ምን ይላል?

"የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን እናውቃለን፣ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፣ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው::" 1ዮሐ 5፣20

     መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ሳይደባብስ በግልጽ ይነግረናል:: ስለዚህ እኛም ቃሉን ልንቀበልና ልናምን ይገባል:: ዛሬ ብዙዎች የእግዚአብሔርን ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ይጠራጠራሉ:: አንተ ግን ወገኔ ሆይ፣ የአምላክህን ቃል ስማ! "እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው::" ብሎ ቃሉ ይነግረናልና::

     የኢየሱስ ክርስቶስን የአምላክነት ባህርይ ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ በሰማያዊ ስፍራ ካሉት መላእክት ሁሉ በላይ መሆኑ ነው:: ምንም እንኳን ሰው ሆኖ ራሱን ዝቅ አድርጎ ይምጣ እንጂ ከመላእክት የሚበልጥ ጌታ ነው::

"ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ ይበልጣል::" ዕብ 1፣4

     የዕብራውያንን መልእክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ባጠቃላይ ስናነብብ፣ ኢየሱስ እጅግ አብዝቶ ከመላእክት እንደሚበልጥ በብዙ ማስረጃ ያሳየናል:: ይህም ብቻ አይደለም፣ በራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ አምስትን በሙሉ ስንመለከት ጌታ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር አብሮ እኩል ሲመለክ እንመለከታለን:: ስዎችና መላእክት ሲያመልኩትና እየወደቁ ሲሰግዱለት፣ ፍጥረታትም ሁሉ ክብርን ሲሰጡት እናያለን:: የአምላክነት አንዱ ባህርይ መመለክ ነውና:: ስለዚህም ኢየሱስ በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጠው እንደ እግዚአብሔር በሰዎችና በመላእክት ሲመለክ ይታያል:: አምልኮና ስግደት በአዲስ ኪዳን ለመላእክት እንኳን የማይደረግ በፍጹም ለአምላክ ብቻ የሚሰጥ ነገር ነውና::

"ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ:: በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ:: እርሱም:- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነብያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፣ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ::" ራእይ 22፣8-9

     ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ጊዜ ግን ብዙ ሰዎች ከእግሩ ስር ወድቀው ሰግደውለታል:: እርሱ ግን ይህን እንዳያደርጉ አንዳቸውንም ሲከለክላቸው አንመለከትም::

"ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት:: እነሆም ለምጻም ቀርቦ:- ጌታ ሆይ፣ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ሰገደለት:: እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና:- እወዳለሁ፣ ንጻ አለው:: ወዲያውም ለምጹ ነጻ::" ማቴ 8፣1-3
    
     "ኢየሱስ ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፣ ሲያገኘውም:- አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው:: እርሱም መልሶ:- ጌታ ሆይ፣ በእርሱ አምን ዘንድ ማነው? አለ:: ኢየሱስም:- አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው እርሱ ነው አለው:: እርሱም:- አምናለሁ አለ፣ ሰገደለትም::" ዮሐ 9፣45-48

     "ቶማስም:- ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት::" ዮሐ 20፣28

"ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ:: እነርሱም ሰገዱለትና በብዙ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፣" ሉቃ 24፣51-52

ሌላው የአምላክነት ባህርይ መፍጠር ነው:: መጀመሪያ ወደተነሳንበት ወደ ዮሐንስ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ስንመለስ እንዲህ የሚል ዓ/ነገር እናገኛለን::

"ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም::" ዮሐ 1፣3

ማናቸውም ፍጥረት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በመፍጠር ሥራ ተካፈይ እንደነበረ የሚያሳይ ክፍል ነው:: ያለ ኢየሱስ አንዳች ነገር ስንኳ እንዳልተፈጠረና እንዳልተከሰተ ይነግረናል:: ይህ እንግዲህ ሕይወት ያላቸውንና የሌላቸውን የምድርን ፍጥረታትና በሰማያዊ ስፍራ ያሉትን መላእክትንም ያጠቃልላል:: ያለ እርሱ የተፈጠረና  በሕይወት የኖረ አንዳች ነገር የለም:: ከዋክብትና ፕላኔቶች፣ ፀሐይና ጨረቃ፣ ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ምድራዊና ሰማያዊ ፍጥረታትን ጨምሮ የተፈጠሩት በክርስቶስ ነው:: ይህም በምድር የነበሩ የሃይማኖት መሪዎችንና ነብያትንም ይጨምራል::

"እርሱ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፣ የሚታዩና የማይታዩትም፣ ዙፋናት  ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ስልጣናት፣ በሰማይና በምድር ያሉ ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና..." ቆላ 1፣15-16

ለፍጥረት መከሰትና መኖር ኢየሱስ ክርስቶስ ዋነኛ ምክንያት ነው:: ሰዎች ይህንንም ያንንም ሊሉ ይችላሉ፣ አንተ ግን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ተስማማ! ቃሉ ምን ይላል?

"ከእነርሱም (ከእስራኤልላውያን) ክርስቶስ በሥጋ መጣ፣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፣ አሜን::" ሮሜ 9፣5

እኛም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አብረን ለእውነቱ አሜን እንበል::

     ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያ ነበረ:: አሜን!
     ኢየሱስ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ:: አሜን!
     ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አምላክ ነው:: አሜን!
     ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋል፣ ያለ እርሱም አንዳች አልተፈጠረም:: አሜን!




የደም መሥዋዕት

pdf version
     እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሊያደርግላቸው ከሚፈልገው ነገሮች ሁሉ ዋናውና ትልቁ ነገር ኃጢአትን ማስወገድ ነው:: ኃጢአት የሰዎች የችግራቸውና የመከራቸው ዋነኛ ሥርና ምክንያት ነውና:: የሕይወትና የበረከት ምንጭ ከሆነው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ያለያያቸውና ያጣላቸው ዋናው ነገር ኃጢአት ነው:: ኃጢአት በሰዎች ታሪክ ሁሉ የሰው ልጆች የሞትና የመከራ፣ የሃዘንና የለቅሶ ምንጭ ነው:: የሰዎችን ከእግዚአብሔር መራቅ ስለዚህም ደግሞ የሕይወት እርካታ አለማግኘታቸውና የመቅበዝበዛቸው፣ እርስ በርስ ፍቅር የማጣታቸው፣ በመጨረሻም ለዘላለም ፍርድና ስቃይ ለሲኦልም የሚያበቃቸው ዋነኛ ክፉ የሰዎች ጠላት ኃጢአት ነው::

     ስለዚህ ኃጢአትን ማስወገድ ለሰው ልጆች ከሚያስፈልጋቸው እርዳታ ሁሉ በፊት በቀደምትነት የሚጠቀስ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው:: ከምግብና ከመጠጥ በፊት ከሥጋ ጤንነት ሁሉ በፊት የነፍስ መዳን ቀዳሚነት ያለው ነገር ነው:: ለዚህም ደግሞ ኃጢአት መወገድ አለበት:: ኃጢአት እያለ ከፍርድ መዳን የለም፣ ኃጢአት እያለ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅና የዘላለም ሕይወት፣ የእግዚአብሔርንም መንግስት መውረስ የለም:: የጥያቄአችን ሁሉ መልስ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ በመጀመርያ ደረጃ የሰው ልጆች የኃጢአት ችግር መፍትሔ ማግኘት አለበት:: ሌላው ሁሉ ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው:: ብዙ ሃይማኖቶች ለዚህ የሰው ልጆች ሁሉ የችግር ሥር ለሆነው ለኃጢአት በቂ መልስ የላቸውም:: አንዳንዶቹ እንዲያውም ፈጽመው አያነሱትም:: ነገር ግን ሰውንና እግዚአብሔርን ለለየው የሰዎች ዋነኛ ችግር መልስ እስካልተገኘ ድረስ የሞተ የሃይማኖት ሥርዓት ብቻ ለሰዎች መፍትሄ አይሆንም::

     ሐኪሞች የሚሰማንን የሕመም ስሜት ስንነግራቸው ሕመማችንን ብቻ ለማስታገስ አይሞክሩም:: ነገር ግን የበሽታችንን መንስኤና ሥር ለማወቅና ለማስወገድ ነው የሚፈልጉት:: እግዚአብሔርም ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ስቃይ ለማስታገስ ብቻ አይሞክርም:: በሰዎች ላይ የምናያቸው መልካም ያልሆኑ ነገሮች ሁሉ አንድ ትልቅና ሥር የሰደደ ችግር እንዳለ ነው የሚያሳየን፣ ይህም የሰው ልጆች ኃጢአት ነው:: መግደልና ማመንዘር፣ ጥላቻና ጠብ፣ ክፋትና ምቀኝነት፣ ስርቆትና ውሸት፣ ስካርና ዝሙት፣ ገንዘብን መውደድና ስስት...ወዘተ እነዚህና የመሳሰሉት ናቸው እንግዲህ የሰው ልጆችን ወደ ጥፋት የሚነዱት፣ የመከራውና የዕንባው መንስኤ የሆኑት፣ ከአምላኩ ያራቁትና ለዘላለም ፍርድ የሚዳርጉት:: የትኛውም ሃይማኖት ለዚህ ጥያቄ መልስ የለውም:: በማንም የሃይማኖት መሪና ነብይ ዘንድ ለኃጢአት መፍትሔ አይገኝም:: የዚህ ምድር የሃይማኖት መሪዎችና ጠቢባን፣ በኃጢአት ምክንያት ለሚደርስብን ሕመም ምናልባት ማስታገሻ ይሰጡን ይሆናል እንጂ ኃጢአትን ራሱን ማስወገድ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው::

     እግዚአብሔር ለመሆኑ ኃጢአትን የሚያስወግደው እንዴት ነው? በተለያዩ የሃይማኖት ሥርዓቶች ነው? የተለያዩ ቦታዎች ሄደው ሰዎች እንዲሰግዱ በማድረግ ነው? ወይስ በጸሎት ርዝመት? በጾምና ራስን በተለያዩ ነገሮች በመጉዳት ይሆን? ወይስ እንዲያው ስለ ኃጢአት ምንም ባለማንሳትና እንደሌለ በመቁጠር?

     በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ (ሊሽር) የሚችል አንድ ነገር ብቻ እንደሆነ እናነባለን::

"የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፣ ደሙም ከሕይወቱ የተነሳ ያስተሰርያልና በመሠዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት::" ዘሌ 17፣11

"...ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም::" ዕብ 9፣22

እግዚአብሔር ለሰዎች ኃጢአት የሰጠው ብቸኛ ማስተሰረያ ደም ነው:: ያለ ደምም የኃጢአት ስርየት የለም:: ደም የሌለው መስዋዕት ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ፣ ሰውንና እግዚአብሔርንም ያስታርቅ ዘንድ ብቁ አይደለም:: ኃጢአት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ድርጊት ነውና:: ኃጢአትን የሚሠራ ሁሉ በራሱ ሕይወት መክፈል አለበት:: ኃጢአት የሠራ ሰው ከሞት ባነሰ ቅጣት አይቀጣም:: ኃጢአት መሥራት በሕይወት ላይ መፍረድ ማለት ነው::

     "የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና..." ሮሜ 6፣23

ከደም በስተቀር ምንም አይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ስግደትና ጾም ረጅምም ጸሎት...ወዘተ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልም::

"የሥጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፣ ደሙም ከሕይወቱ የተነሣ ያስተሰርያልና..." ዘሌ 17፣11

ስለዚህም በብሉይ ኪዳን ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ ኃጢአታቸው ይሰረይ ዘንድ የተለያዩ የከብቶች መስዋዕትን ለእግዚአብሔር ማቅረብ ነበረባቸው::

"...ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔርም:- አትስሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ ...ስለ ሠራው ስለ ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኃጢአት መስዋዕት ያቀርበዋል:: ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፣ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፣ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል:: የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፣ ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል::" ዘሌ 4፣2-6

በብሉይ ኪዳን ማንኛውም ሰው ለኃጢአት መሥዋዕትን ሲያቀርብ ሊያስተውል የሚገባው ሶስት ዋና ዋና ነገሮች አሉ::

     በመጀመሪያ የሚቀርበው መስዋዕት ነውር የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ ነው:: ይህም ማለት የሚቀርበው እንስሳ፣ አንካሳ ወይም እውር ያልሆነ ወይም የቆዳ በሽታ የሌለበትና ፍጹም ጤነኛ መሆኑን ማረጋገጥ ነው:: ምክንያቱም ነውር ያለበትን መስዋዕት ለእግዚአብሔር ማቅረብ በጥብቅ የተከለከለ ነው:: ቢቀርብም ኃጢአትን ሊያስተሰርይ አይችልም::

"በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነውና ነውር ወይም ክፉ ነገር ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋ::"
ዘዳ 17፣1

"ነውረኛ ወይም አንካሳ ወይም ዕውር ቢሆን፣ ወይም አንዳች ክፉ ነውር ቢኖረው ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋው::" ዘዳ 15፣21

ስለዚህ ማንኛውም ሰው ለመሥዋዕት የሚያቀርበው እንስሳ አንዳች ነውር እንደሌለው ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው:: ለመሥዋዕት የሚቀርበው እንስሳ ነውር የሌለው ንጹህ መሆኑ ከተረጋገጠ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወደ መሠዊያው ያመጣዋል:: በድብቅ የሚታረድ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውምና::

     በሁለተኛ ደረጃ እንስሳውን ወደ መገናኛው ድንኳን ካመጣ በኃላ የሚቀጥለው ድርጊት ኃጢአት የሠራው ሰው እጁን በወይፈኑ ላይ መጫን ነው:: ይህም ሰውዬው የሠራውን ኃጢአት እንስሳው እንደሚሸከም የሚያሳይ ነው:: የሰውዬውን ኃጢአት የተሸከመው እንስሳ እንግዲህ ሰውዬው ሊቀበለው የነበረውን የሞት ፍርድ ይቀበላል ማለት ነው:: ስለዚህም በእርሱ ፋንታ እንስሳው ይታረዳል::

     በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ካህኑ የከብቱን ደም ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ይረጨዋል:: ይህም እግዚአብሔር መሥዋዕቱን እንደተቀበለና የሰውዬውም ኃጢአት እንደተሰረየለት፣ ሰውዬውም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን እንደተቀበለ ያመለክታል:: ይህንንም ሥርዓት ኃጢአት በሠሩ ቁጥር ያደርጉ ነበር::

     "...ደምም ሳይፈስ ስርየት የለምና"

     ነገር ግን በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር የዓለምን ኃጢአት ሁሉ በአንድ ጊዜ የሚያስወግድ የራሱን በግ ነው ያዘጋጀልን:: እርሱም ሰማያዊው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::

"በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፣ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ::" ዮሐ 1፣29

ኃጢአትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: በብሉይ ኪዳን ለመሥዋዕት ይቀርቡ የነበሩት ኮርማዎችና ፍየሎች በጎችም ሁሉ የእውነተኛው የእግዚአብሔር በግ የኢየሱስ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው እንጂ ኃጢአትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ አይችሉም::

"ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፣ እርሱ (ኢየሱስ) ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ" ዕብ 10፣11-12

ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ የሆነ መሥዋዕት፣ ይኸውም ራሱን በማቅረቡና ደሙን በማፍሰሱ ለሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአት ስርየት ብቸኛ መንገድ ነው:: ከእግዚአብሔር በግ በስተቀር ኃጢአትን ሊያስወግድ የሚችል ምንም ነገር የለም::

     ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰዎች ኃጢአት ከመሠዋቱ በፊት ልክ እንደ ብሉይ ኪዳን መስዋዕቶች ነውር የሌለበት መሆኑ መረጋገጥ ነበረበት:: ነውር የሚያመለክተው ኃጢአትንና መተላለፍን በእግዚአብሔር ፊትም መርከስንና ተቀባይነት ማጣትን ነው:: ኢየሱስ ግን ያለ ኃጢአት የኖረ በመሆኑ ለመሥዋዕትነት ብቁ ነው:: ኢየሱስ በኖረበት ዘመን የነበሩ የእርሱ ተቃዋሚዎች ፈልገውና መርምረው ያላገኙት ነገር ኃጢአት ነው:: ስለዚህም ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ብሎ ይጠይቃቸው ነበር:-

     "ከእናንተ ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው?" ዮሐ 8፣46

ማነው እየሱስን ስለ ኃጢአት የሚወቅስ? ኃጢአት ሠርቷል ብሎ ወደ ኢየሱስ እጁን የሚጠቁም ማን ነው? ስህተትና ነውር ተገኝቶበታል ብሎ በኢየሱስ ላይ የሚነሳ ማን ነው? በሰማይም በምድርም ኢየሱስን ስለ ኃጢአት የሚወቅስ ማንም የለም:: በምድርም ላይ ያለአንዳች ኃጢአት (ነውር) የኖረ ብቸኛ ሰው እርሱ ብቻ ነውና::

"እርሱም ኃጢአት አላደረገም፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም..." 1ኛ ዼጥ 2፣22-23

ኢየሱስ ነውርና ነቀፋ የሌለበት የሰው ልጆችን ኃጢአት ሊያስተሰርይ የሚችል የእግዚአብሔር በግ ነው ! የሌላ ሰው ደም ግን እንኳን የዓለምን ይቅርና የራሱንም ኃጢአት ሊያስተሰርይ አይችልም::

"ልዩነት የለምና፣ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል..." ሮሜ 3፣22-23

ሌላው ልክ የብሉይ ኪዳን እንስሳት እጅ ተጭኖባቸው የሰውን ኃጢአት እንደሚሸከሙ፣ ኢየሱስም የሰዎችን ኃጢአት መሸከም ነበረበት:: አንድ ከብት የሚሸከመው የአንድን ሰው ኃጢአት ብቻ ነበረ፣ ኢየሱስ ግን የዓለምን ኃጢአትና በደል ሁሉ በራሱ ላይ ተሸክሞ በእኛ ፋንታ መከራንና ሞትን ተቀበለ:: ለእኛም ሲል ተሠዋ::

     "...እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ::"
ኢሳ 53፣6
"...ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፣ ኃጢአታቸውንም ይሸከማል::" ኢሳ 53፣11
"...እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ..." 1ዼጥ 2፣24

ነውርና እንከን የሌለበት የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ ብቸኛ የመስዋዕት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: አምላክ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣበት ዋነኛ ምክንያት እንግዲህ ለችግራችን መንስኤ መፍትሔ ለመስጠት ነው::

"...እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ::" ! ዮሐ 1፣29

     ኢየሱስ መስዋዕት ሲሆንና ለእኛም ደሙን ሲያፈስ በድብቅና በድንገተኛ ሞት አልነበረም:: ነገር ግን ነግሥታትና የሃይማኖት መሪዎች፣ ካህናቱም ሕዝቡም ሁሉ እያወቁና እያዩ በእግዚአብሔር ፊት መስዋዕት ሆነ:: ንጹህ የሆነውንም ደሙን አፈሰሰልን::

     በመጨረሻም በብሉይ ኪዳን የከብቶችን የመሥዋዕት ደም ሊቀ ካህናት ወስዶ ወደ እግዚአብሔር እንደሚያቀርብና የመገናኛውንም ድንኳን እንደሚረጭ፣ የመሥዋዕት በግም ሊቀካህናትም የሆነው ኢየሱስ ከሙታን በመነሳት የራሱን ደም ይዞ ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር መኖሪያ ወደ ሰማይ በመሄድ በደሙ ይቅርታንና የኃጢአትን ስርየት ከእግዚአብሔር ዘንድ አስገኘልን:: እግዚአብሔርም ይህንን መሥዋዕት በደስታ ተቀብሎታል:: ኢየሱስ አንዳች ተጨማሪ የማያስፈልገው የዓለምን ኃጢአት ሁሉ የሚያነጻና ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ በቂ የመሥዋዕት በግ ነው::

     ከጥንት ጀምሮ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የተስተካከለ ግንኙነት ለማድረግ የተለያዩ መሥዋዕቶች ያቀርባሉ:: አንዳንዶች እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሌሎችም በራሳቸው የገመቱትንና የመሰላቸውን ያቀርባሉ:: ቁም ነገሩ ግን እግዚአብሔር መሥዋዕትን ሁሉ ይቀበላል ወይ? ለኃጢአት ስርየት ይሁን ወይም ወደ እርሱ ለመቅረብ በሚደረግ ድርጊት ሁሉ እግዚአብሔር ደስ ይሰኛል ወይ? ልንጠይቅ የሚገባን ዋና ነገር ይሄ ነው::

     በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረቡት አቤልና ቃየን የተለያዩ መሥዋዕቶችን እንዳቀረቡ እንመለከታለን::

"ከብዙ ቀንም በኋላ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፣ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ::"
ዘፍ 4፣3-4

አቤልም ቃየንም መሥዋዕትን አቅርበዋል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የሁለቱንም መሥዋዕት ይቀበላል ወይ? መሥዋዕቶቻቸውም፣ አንዱ በውስጡ ደም ያለው የሚንቀሳቀስ በግ፣ ሌላውም በድን የሆነ የምድር ፍሬ፣ እግዚአብሔር በሁለቱም መሥዋዕቶች ይደሰታል ወይ? አይኖቹስ ወደ ሁለቱም ይመለከት ይሆን?

"እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፣ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም:: ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ::" ዘፍ 4፣4-5

ሰዎች እንደመሰላቸው ወደ ሚያቀርቡት መሥዋት ሁሉ እግዚአብሔር አይመለከትም:: ለኃጢአት ሥርየት የማይሆን በድን መሥዋዕትን እግዚአብሔር አይቀበልም:: ለኃጢአታችን ሥርየት ይሆናል፣ ወደ እግዚአብሔርም ያቀርበናል ብለን እንደፈቃዳችን በምናደርገው ድርጊት ሁሉ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም::

     "...ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም::" !

     ኃጢአትን ያስተሰርያል ብለን ወደምናቀርበው፣ ወደ ሞተና በድን ወደ ሆነ የተለያየ የስግደትና የጸሎት ሥርዓት ሁሉ እግዚአብሔር አይመለከትም ! ነገር ግን ሕያው ወደ ሆነ፣ ነውርና እንከን ወደ ሌለው የደም መሥዋዕት እግዚአብሔር ይመለከታል::

     አንተስ ለኃጢአት ስርየት በእግዚአብሔር ፊት የምታቀርበው መሥዋዕት ምንድነው? የሞተ የሃይማኖት ሥርዓት ነው? ወይስ የተለያዩ መልካም የሚመስሉ የሰው ሥራዎች? ወገኔ ሆይ፣ እግዚአብሔር ወደዚህ አይመለከትም ! አንተም እንደ አቤል የደም መሥዋዕት ያስፈልግሃል:: አንተንም እንደ አቤል የበግ መሥዋዕት ያስፈልግሃል:: እግዚአብሔር የተመለከተውና የተቀበለው የደም መሥዋዕት እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ያስፈልግሃል::

     እነሆ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ !

     በአዲስ ኪዳን ኮርማዎችንና ፍየሎችን ለእግዚአብሔር አናቀርብም:: ነገር ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነውር የሌለው የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ስለ ኃጢአታችን ታርዷል:: ዛሬ እግዚአብሔር፣ ራሱ ካዘጋጀው በግ ከኢየሱስ ሌላ ወደ ማናቸውም መሥዋዕቶች አይመለከትም፣ በየትኛውም ደስ አይሰኝም፣ በእርሱም ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም:: እግዚአብሔር ኢየሱስ ከሙታን አስነስቶ በራሱ ቀኝ ያስቀመጠውም የኢየሱስን መሥዋዕትነት ስለተቀበለ ነው::

"...እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መስዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ" ዕብ 10፣12

     እንደ ቃየን በበድን መሥዋዕት አትታመን ! ሊያድን በማይችል የሃይማኖት ሥርዓትና የሰው ፍልስፍና ተስፋ አታድርግ ! ነገር ግን የዓለምን ኃጢአት ሁሉ በሚያስወግደው በኢየሱስ ተማመን ! በእርሱ የሚያምን አያፍርምና::

No comments:

Post a Comment